የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም በዓለ ልደት
ሙሽራዬ ሆይ ከሊባኖስ ከኔ ጋራ ነዪ:: መኀ. 4፥ 8

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ምእመናን በሥላሴ ስም እንደምን አደራችሁ?
በያላችሁበት ቦታ የመድኀኔዓለም ቸርነት የእመቤታችን በረከት የቅዱሳን መላእክት ጥበቃ አይለያችሁ!
እንኳን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዓለ ልደት በሰላም በጤና አደረሳችሁ!
አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም እንደተናገረው ” እግዚአብሔር አብ በሰማይ ሆኖ ምሥራቅና ምዕራብን ሰሜንንና ደቡብን ዳርቻዎችንም ሁሉ በእውነት ተመለከተ ተነፈሰ አሻተተም እንዳንች ያለ አላገኘም የአንችን መዓዛ ወደደ ደምግባትሽንም ወደደ የሚወደውን ልጁንም ወደ አንች ሰደደ። ” በማለት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለሰው ልጆች ድኅነት በእግዚአብሔር ልቡና ታስባ የኖረች ለሰው ልጆች ሁሉ የመመኪያ ዘውድ ሆና መገኘቷና ያስረዳናል።
ድንግል ማርያም ከቅዱሳን ቤተሰቦቿ ከሐና ከኢያቄም የተፀነሰችው የተወለደችው በመንፈስ ቅዱስ ተጠብቃ የኖረችሁ በብቸኝነት የእግዚአብሔር ወልድ ማደሪያ በሥጋ መገለጫ ሆና እኔ እና እናንተ የሥላሴን ልጅነት እንድናገኝ እና በሥጋ ወደሙ መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ ነው።
የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምልጃና ጸሎት አይለያችሁ መልካም በዓል ይሁንላችሁ!!!
