የቅዱስ ሚካኤልና የቅዱስ ላሊበላ ዓመታዊ በዓል
🕊️ እንኳን ለቅዱስ ሚካኤልና ለቅዱስ ላሊበላ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ! 🕊️
“ከጽንፍ እስከ ጽንፍ የሚበር፤ ንሥረ አርያም የሚባል፥ ውዳሴው እንደ ማር የጣፈጠ፥ ንዑድ ክቡር የሆነ የቅዱሳን መላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ነው፡፡”
ሰኔ ፲፪ ቀን የምሕረትና የረድኤት መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ፭ (አምስት) ታላላቅ ተአምራትንና ምሥጢራትን የፈጸመበት፤ እንዲሁም የቅዱሳን ታላቅ መታሰቢያ ዕለት ነው፡፡
🌟 በዕለቱ የተፈጸሙ ፭ቱ የቅዱስ ሚካኤል ድንቅ ነገሮች
፩. በዓለ ሲመቱ፦ አምላክነትን ሽቶ ከወደቀው ከሳጥናኤል ምትክ፤ በፈቃደ እግዚአብሔር የኃይላት አለቅነቱን እንደያዘ በአጠቃላይ ለ፺፱ኙ (99ኙ) ነገደ መላእክት አለቃ (ሊቀ መላእክት) ሆኖ የተሾመበት ዕለት ነው፡፡
፪. የቅድስት አፎምያ መዳን፦ የአስተራኒቆስ ሚስት ቅድስት አፎምያን ከሰይጣን ተንኮል ያዳነበትና የቅድስት አፎምያም በዓለ ዕረፍቷ በዚህ ዕለት ነው፡፡
፫. የባሕራን መዳን፦ ርኅራኄ ከሌለው ባለጸጋ ተንኮልና ሞት፤ ሕፃኑን ባሕራንን በድንቅ ተአምር ያዳነበት ዕለት ነው፡፡
፬. የእለ እስክንድሮስ ቅዳሴ ቤት፦ በግብፅ ሀገር 312-326 ዓ.ም የነበረው ፓትርያርክ እለ እስክንድሮስ “ሳተርን” የተባለውን የጣዖት ቤት አፍርሶ፤ በቦታው ላይ ቤተ ክርስቲያን ሠርቶ ታቦተ ሚካኤልን ያገጠመበትና ቅዳሴ ቤቱን ያከበረበት ነው፡፡
፭. የቅዱስ ላሊበላን ነፍስ ወደ ሰማይ መንጠቁ፦ የኢትዮጵያ ንጉሥ ቅዱስ ላሊበላን ወደ ሰማያት ነጥቆ ወስዶ የሰማያዊውን መቅደስ አሠራርና ምሥጢር ያሳየበት ዕለት ነው፡፡
⛪ የሌሎች ቅዱሳን መታሰቢያ
*ንጉሥ ቅዱስ ላሊበላ፦ *በሰማያት ያለውን ምሥጢር አይቶ ውቅሮቹን አብያተ ክርስቲያናት ያነጸው ጻድቁ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ቅዱስ ላሊበላ በዓለ ዕረፍቱ በዚህ ዕለት ነው፡፡
*አባ ቄርሎስ*፦ 67ኛው የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ዕረፍቱ ነው፡፡
*አባ ዮስጦስ*፦ በቅዱስ ማርቆስ እጅ የክርስትና ጥምቀትን ያገኘው፣ ዲቁናና ቅስና የተሾመው 6ኛው የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ዕረፍቱ ነው፡፡
📖 ከዕለቱ ታሪክ የተማርነው (ስለ ባሕራን አባትና ስለ ባለጸጋው)
“ለድኃ ከመመጽወት ቸል አትበይ፤ የቅዱስ ሚካኤልንም በዓል በየወሩ ከማክበር አትቦዝኝ!”
እግዚአብሔርን የሚፈራው የባሕራን አባት ለባለቤቱ የተወው ይህ አደራ፤ ዛሬም ለእኛ ታላቅ ትምህርት ነው፡፡ ክፉው ባለጸጋ በምቀኝነት ሕፃኑን ባሕራንን በሣጥን ውስጥ ከቶ ወደ ባሕር ቢጥለውም፤ የቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነት ግን ባሕራንን ከሞት አድኖ “የባሕር ስጦታ” አድርጎታል፡፡ የሰው ክፉ ምክር በእግዚአብሔር ፊት ከንቱ ነው!
መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ካለንበት የክፉዎች ወጥመድና ከተንኮል ሁሉ በክነፎቹ ጋርዶ ያውጣን፤ የጻድቁ ንጉሥ የቅዱስ ላሊበላ በረከትና ረድኤት ከሁላችን ጋር ይሁን!
*ወስብሐት ለእግዚአብሔር *
