መንፈሳዊ አገልግሎቶች
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።
በቼክ ሪፐብሊክ የቅዱስ ሚካኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማኅበር፣ ምዕመናን በሃይማኖት ጸንተው፣ በምግባር ታንጸው፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሥርዓትና ትውፊት ጠብቀው እንዲኖሩ የበኩሉን ጥረት እያደረገ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናችንን በሙሉ አቅም የማቋቋም ሒደት ጅማሮ ላይ ስለምንገኝ፣ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን መንፈሳዊ አገልግሎቶች ከካህናት አባቶች፣ ከማኅበረሰባችን እና በአቅራቢያችን ካሉ እህት አብያተ ክርስቲያናት ጋር በመተባበር እናስተባብራለን። ወደፊትም የራሳችንን ቋሚ የአገልግሎት ሥፍራ በመያዝ እነዚህን አገልግሎቶች በስፋት እና በቋሚነት ለመስጠት እንጥራለን።
በዋናነት የምናስተባብራቸው አገልግሎቶች
1. ሥርዓተ ቅዳሴ እና ጸሎት በካህናት አባቶች እየተመራን፣ የቦታ ሁኔታዎችን በማመቻቸት በዐበይት በዓላት እና በተመረጡ ቀናት ምዕመናን ተገኝተው የሥርዓተ ቅዳሴ፣ የኪዳን እና የጸሎት መርሐ ግብሮች ተካፋይ እንዲሆኑ እናስተባብራለን።
2. የምሥጢራት አገልግሎት ማመቻቸት፦ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓትን በጠበቀ መልኩ ምዕመናን የቤተ ክርስቲያን ምሥጢራትን (ሥርዓተ ጥምቀት፣ ሥርዓተ ተክሊል/ጋብቻ፣ እና ሥርዓተ ቁርባን) ማግኘት እንዲችሉ ከካህናት ጋር በማገናኘት ሁኔታዎችን እናመቻቻለን።
3. የንስሐ አባት፦ እያንዳንዱ ምዕመን በንስሐ አባት እየታገዘ መንፈሳዊ ሕይወቱን እንዲመራ፣ ከኃጢአት ነጽቶ በንስሐ እንዲመለስ፣ እንዲሁም መንፈሳዊ ምክር እንዲያገኝ የንስሐ አባቶችን እንዲያገኙ ከአባቶች ጋር በመነጋገር እናግዛለን።
4. ትምህርተ ወንጌል እና የሰንበት ትምህርት ቤት፦ ወደፊት ቋሚ የሰንበት ትምህርት ቤት በማቋቋም ሕፃናት፣ ታዳጊዎች እና ወጣቶች የቤተ ክርስቲያንን ዶግማ እና ቀኖና እንዲማሩ ለማድረግ ፀሎታችን ነው። በአሁኑ ሰዓትም ምዕመናን በእግዚአብሔር ቃል እንዲታነጹ ልዩ ልዩ የትምህርት እና የጸሎት መድረኮችን እናዘጋጃለን።
ወቅታዊ የአገልግሎት መርሐ ግብሮች
በአሁኑ ወቅት ቋሚ የሆነ ዕለታዊ/ሳምንታዊ የአገልግሎት ቦታ እና ሰዓት በማዘጋጀት ላይ ስለምንገኝ፣ ሥርዓተ ቅዳሴ የሚካሄድባቸውን ቀናት፣ የጸሎት እና የትምህርት መርሐ ግብሮችን (ቦታ እና ሰዓት) በቅድሚያ በድረ-ገጻችን እና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን እናሳውቃለን። ዝግጅቶቻችንን በንቃት እንድትከታተሉ በእግዚአብሔር ስም እናሳስባለን።
የማኅበሩ/የአጥቢያው አባል ይሁኑ
ይህንን ጅማሮ ከዳር በማድረስ በቼክ ሪፐብሊክ የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያንን በቋሚነት ለመትከል እና መንፈሳዊ አገልግሎቶችን ለማስፋፋት የሁላችንም ርብርብ፣ ጸሎት እና አንድነት ያስፈልጋል። የዚህ ቅዱስ ዓላማ ተካፋይ እና የማኅበራችን አባል በመሆን የበኩልዎን መንፈሳዊ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ በእግዚአብሔር ስም እንጠይቃለን።
